የፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ መልቀቂያ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በራሳቸው ፍቃድ ከሀላፊነታቸው ለቀቁ።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የስራ መልቀቂያቸውን በዛሬው እለት በካሄደው 2ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ በማቅረብ ነው ሀላፊነታቸውን የለቀቁት።

ፕሬዚዳንቱ መልቀቂያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ በርእሰ ብሄርነት ያገለገሉባቸው ያለፉት 5 ዓመታት በህይወት ጉዟቸው ትልቅ ቦታ የሚይዝ መሆኑን ተናግረዋል።

“የምወደውን ህዝብ እና ሀገር መገልገል በመቻሌ ትልቅ ክበር ይሰማኛል” ያሉት ዶክተር ሙላቱ፥ “የተሰጠኝን ሀላፊነትን በታማኝነት እንደተወጣው ይሰማኛል” በማለት፤ ለዚህ እንድበቃ ላደረጉኝ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትም ከፍተኛ መስጋና አቀርባለው” ብለዋል።

በፕሬዚዳንትነት ካሳለፏቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ሶስቱ ዓመታት ሀገሪቱን በአመዛኙ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወድቃ የነበረችበት እና ብሄራዊ ደህንነቷ ላይ ትልቅ ስጋት ተጋርጦ እንደነበረ አንስተዋል።

ይህም የዜጎችን የዴሞክራሲ፣ የልማት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የህግ የበላይነትን ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ባለመቻሉ በህዝቡ ዘንድ በተቀሰቀሰ ቁጣ የመጣ እንደነበረም አስታውሰዋል።

“ዛሬ ግን በተለይም ግን ከስድስት ወራት ወዲህ በሀገራችን የተስፋ ጎህ ቀዷል ማለት ይቻላል” ሲሉም ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ዓለምን ያስደመሙ ለውጦች በሀገሪ እየመጡ ነው ያሉት ዶክተር ሙላቱ፥ በውጭ ሀገራት የነበሩ የፖለቲካ ሀይሎች ወደ ሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ መደረጉና የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ዳግም መታደስም ከለውጦቹ ውስጥ ትልቁን ስፍራ የሚይዙ ስኬቶች ናቸው ብለዋል።

ዶክተር ሙላቱ፥ እነዚህ ስኬቶች ሊያዘናጉን አይገባም፤ ይልቁንም የተገኙትን ስኬቶች የበለጠ ከፍ ለማድረግ ጠንክረን መስራት አለብን ብለዋል።

ሀገሪቱን ከድህነት ማላቀቅ፣ ልማትን ማረጋገጥ እና የዴሞክራሲ ስርዓትን ማስፈን አሁንም ቢሆን መንግስት ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ ነው ያሉት ዶክተር ሙላቱ፥ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትን የሀግ ማእቀፎችን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ስራዎች እየተተገበሩ እንደሆነም አንስተዋል።

ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በመጨረሻም፥ “በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየታየ ላለው ለውጥ አንድ አካል በመሆኔ ከፍተኛ ደስታ እንዲሰማኝ አድርጓል” ያሉ ሲሆን፥ “የሚሰጠኝ ተስፋም ትልቅ ነው” ብለዋል።

“ዛሬ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል የሚችሉ፣ ቁርጠኝነትን የተላበሱ አመራሮችን ማግኘቷ ደስታ ፈጥሮብኛል” ሲሉም ተናግረዋል።

“በዚህም መሰረት ላለፉት አምስት ዓመታት ይዤ የቆየውተን ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊነት ለቀጣዩ ትውለድ ለማስተላለፍ ውሳኔ ላይ የደረስኩ ስለሆነ የተከበረው ምክር ቤት ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትነት ሀላፊነቴ እንዲያሰናብተኝ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቶቹም በዛሬው እለት ባደረጉት ሁለተኛ የጋራ ስብሰባ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ያቀረቡትን የስራ መልቀቂያ ተቀብለዋል።

በሙለታ መንገሻ

© 2020 Sidama Media Network All rights reserved.